የኢሠማኮ አሠራርና መዋቅር የሚለውጥ ሐሳቦች በቅርቡ ለውሳኔ ይቀርባል

አቶ ካሣሁን ፎሎ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (አሠማኮ) ፕሬዝዳንት
የአገር አቀፍ ኃይል ማመንጫ፣ ኬሚካልና ማዕድን ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ባለፈው መስከረም 25 ቀን ለጠራው 39ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ በባለሙያዎች ያስጠናው የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ እቅድ የኮንፌዴሬሽኑን አሠራርና አወቃቀር የሚያሻሽሉ ሃሳቦች እንደተካተቱበትና ለቀጣዩ ጠቅላይ ምክር ቤት ውሳኔ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ በማስከተልም የዝቅተኛ መነሻ የደመወዝ ወሳኝ ቦርድ ማቋቋሚያ ደንብ ከመንግሥትና ከአሠሪ ጋር በመወያየት ተዘጋጅቶ ለውሳኔ እንደቀረበና የሠራተኛውን ሃሳብ ለማካተት እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በእለቱም የአገር አቀፍ ኃይል ማመንጫ፣ ኬሚካልና ማዕድን ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ መንገሻ ደሴ በሥራ ሪፖርታቸው ፌዴሬሽኑ ባለፈው በጀት ዓመት አሥር አዳዲስ ማኅበራት እንዳደራጁ፣ በአሥራ ሁለት ማኅበራት የኢንዱስትሪ ግንኙነት ክትትል ሥራዎች እንዳከናወነ፣ ስምንት ማኅበራትን በአካል ተገኝቶ እንደጎበኘ፣ በሁለት ማኅበራት የሴቶች ኮሚቴዎች እንዳቋቋመና ለዘጠና የማኅበር አመራሮች የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠናዎች እንደሰጠ ዘርዝረዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ጨምረውም ፌዴሬሽኑ ከኢንዱስትሪ ኦል የአፍሪካ ከሰሐራ በታች ቀጠና ጋር ያለው ግንኙነት መጠናከሩን ጠቅሰው፣ በቀጣይ የበጀት አመት አሥር አዲስ ማኅበራት ለማደራጀት፣ አምስት የሴቶች ኮሚቴ ለማቋቋም፣ አሥር ማኅበራትን ለመጎብኘት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን ለማሳደግ መታቀዱን አስታውቀዋል።