በእርሻ ስራዎች ላይ በተለይ በቡና እርሻ ላይ ምቹና አካታች የስራ ሁኔታና የስራ አካባቢን በተመለከተ አውደ ጥናት ተደረገ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) ኢስኮስ ኤሚሊያ ሮማኒ ከተባለ የጣሊያን የሠራተኛ ማኅበር ተቋም ጋር በመተባበር በእርሻ ስራዎች ላይ በተለይ በቡና እርሻ ላይ ምቹና አካታች የስራ ሁኔታና የስራ አካባቢን በተመለከተ የተደረገ አውደ ጥናት ላይ መስከረም 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል፡፡በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ አቶ ካሳሁን ፎሎ የኢሠማኮ ፕሬዛዳንት እንደተናገሩት ኢሠማኮ በተለያዩ ወቅቶች ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የሠራተኛ፣ የሠራተኛ ማኅበራት፣ የስራ ሁኔታ እና መሰል ጥናቶች ዙርያ ጥናቶች እንደሚያስጠና ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ጥናቶች ትኩረታቸው በአብዛኛው የሠራተኛው ሙቹና ኣካታች የስራ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡ የዛሬው አውደ ጥናትም እንዲሁ በእርሻ ስራ ላይ በተለይም በቡና እርሻ ላይ ያተኮረ መሆኑ በዘርፉ ላይ ተሰማርተው ያሉ ሠራተኞች እየሠሩ ባሉባቸው የሥራ ቦታዎች ላይ መብታቸው እንዲከበር፣ ሙቹ እና የተረጋጋ የስራና የኑሮ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን በማየት ይህን ለማሻሻል የሚያስችል ስራ ለመስራት እንዲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጥናቶቹ በኦሮምያ ክልል ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች በሚገኙ የቡና እርሻዎች እንዲሁም በጅማ አካባቢ በሚገኙ የቡና እርሻዎች ላይ የተሰራ ነው፡፡ በአውደ ጥናቱ ላይ በተሰጠው ርእሰ ጉዳይ ምርምርና ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች የጥናታቸውን ውጤት አቅርበዋል፡፡