የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)
የጠቅላይ ምክር ቤት 47ኛው መደበኛ ስብሰባ ተጀመረ

53 አዲስ ማኅበራት ተደራጅተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) 47ኛው መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ መስከረም 26 እና 27 ቀን 2014 ዓ/ም በኢሠማኮ ሆቴል ካምፖ አሥመራ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የ2013 የበጀት ዓመት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና የኦዲት ኮሚቴ ሪፖርቶችን በመስማት ተጀመረ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች የሚገኙ የሠራተኞችን ችግሮች ከመፍታት አንጻር የተሠሩት ሥራዎች፣ 53 አዲስ ማኅበራት መደራጀታቸውን፣ ከተለያዩ ደጋፊ ተቋማት ጋር በተባበር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለ2244 የማኅበር አመራሮች ስልጠና መስጠቱን፣ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ በኢሠማኮ፣ በኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኖችና መሠረታዊ ማኅበራት 7,069,775 ብር ቦንድ ግዢ መደረጉን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም የኮንፌዴሬሽኑን እንቅስቃሴ ለሌሎች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ስለተከናወኑ ሥራዎች እንዲሁም የሕግና የምክር አገልግሎት ድጋፎች መከናወን መቻሉን በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ኦዲት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኦላኒ ሴቄታ በ45ኛው እና በ46ኛው የምክር ቤት ጉባዔዎች በአስተዳደር መምሪያ እና ፋይናንስ መመሪያ ዙሪያ የተገኙ የምልከታ ግኝቶች እና በ2013 የበጀት ዓመት የሥራ አስፈጻሚ እንቅስቃሴዎች የተስተዋሉ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ትኩረት በማድረግ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በሁለት ቀናት ውሎው የኢሠማኮን የተደራሽነት ጥያቄ ለመመለስ የቀረበ ጥናት ላይ ተወያይቶ ማጽደቅ፣ የ2013/14 የሥራና የበጀት እቅድ ላይ ተወያይቶ ማጽደቅ፣ የኢሠማኮ ተመራጮች አስተዳደር መምሪያ ላይ ተወያይቶ ማጽደቅ እና ሌሎችም አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡