ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየት እንደሚፈልጉ ሠራተኞች ተናገሩ

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሞ ባህል ማዕከል ባዘጋጀው ዓለምአቀፉ የሠራተኞች ቀን በዓል ላይ ታዳሚ የሆኑ ሠራተኞች የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በመላው አገሪቱ በየደረጃው የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አግኝተው ያነጋገሩ ቢሆንም ሠራተኛውን ግን እስካሁን ያላነጋገሩ በመሆኑ ጊዜ መድበው ከሠራተኛው ጋር  ውይይት እንዲያደርጉ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ በበዓሉ ላይ በነበረው የውይይት መርሀግብር ከተለያዩ ተቋማት የመጡ እነዚሁ ሠራተኞች እንዳነሱት የኢትዮጵያ ሠራተኞች በአገሪቱ ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ናቸው፡፡ሠራተኛው በታማኝነት ግብሩን የሚከፍል ቢሆንም እውቅና እንኳን ለማግኘት ያልቻለ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

በኑሮ ውድነትና ሌሎች ችግሮች እየተሰቃየ የሚገኘውን ሠራተኛ ችግሩን በቅርበት ለማወቅና ለማነጋገር እንኳን መድረክ እንዳልተመቻቸለት አስቀምጠዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ በተለይ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡  

እነዚህ ሠራተኞች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ሁሉ አገራቸውን በማስቀደም ተቋቁመው እና ቅድሚያ ለአገራቸው ሰጥተው የሚገኙ ቢሆንም እነሱን ቀርቦ ያሉባቸውን ችግሮች ለመረዳትና ለማነጋገር ግን መድረክ ሊመቻች እንዳልተቻለ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በተለያዩ መድረኮች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ስላሉ ችግሮች ሲወያዩና መፍትሔ ሲፈልጉ የሚታይ ቢሆንም የሠራተኛውን ክፍል ግን ሊያገኙት አለመቻላቸው እንዳሳሰባቸው አስረድተዋል፡፡

በዚህ በዓል የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል፣የሁለቱ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንና ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም የዓለም ሥራ ድርጅት ተወካይ ንግግር አድርገዋል፡፡ በቀጣይ የ‹‹ሠራተኛው ድምጽ›› እትማችን በዓሉን በተመለከተ ሰፊ ዘገባ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡