ኤች አይ ቪ/ኤድስ/ እንደሌለ በመቆጠሩ ከባድ መዘናጋት እየታየ መሆኑ ተገለጸ

ኤች አይ ቪ/ኤድስ/ እንደሌለ በመቆጠሩ ከባድ መዘናጋት እየታየ መሆኑ ተገለጸ

ኤች አይ ቪ/ኤድስ/ እንደሌለ በመቆጠሩ ከባድ መዘናጋት እየታየ መሆኑ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን /ኢሠማኮ/ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከዓለም ሥራ ድርጅት ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚከበረውን  የፀረ ኤች አይ ቪ/ኤድስ/ቀን ህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳራሽ ባከበረበት ወቅት ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ36ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ “የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይቪ መከላከል’ በሚል መሪ ቃል ሲከበር፤ የኢሠማኮ የማህበራዊ ጉዳይ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሀፅዮን ቢያድግልኝ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በኤች አይቪ ዙሪያ በነበረው የተዛባ አመለካከት የተነሳ ይደርስ የነበረው የማግለል ተፅዕኖ ቢቀንስም በተቃራኒው በሽታው እንደሌለ ተቆጥሮ ከባድ መዘናጋት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በሽታው እያጠቃው ያለው በአምራች የእድሜ ክልል ውስጥ ያለውን ኅብረተሰብ ክፍል በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተከታታይ የሆነ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በመርሀ-ግብሩ የኤች አይቪ/ኤድስ/ ቀንን ለምን እናከብራለን በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢሠማኮ ማኅበራዊ ጉዳይ ባለሙያ ወ/ሮ ሰርካለም ሽፈራው ስለ በሽታው ያለንን ግንዛቤን ለማሳደግ እና ሁሉም ዜጋ ከኤች አይ ቪ የመጠበቅ ፣የመመርመር ህክምና እና እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳለው ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ገልጸው፤  በአሁኑ ወቅት በሀገራችን  ያለውን የኤች አይቪ/ኤድስ/ ስርጭት በሚመለከትም ቁጥሩ የቀነሰ ቢመስልም የመመርመርና ራስን የማወቅ ሁኔታው በጣም ስለቀነሰ በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ መዘናጋት አለ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴርን ወክለው በዕለቱ መልእክታቸውን ያስተላለፉት አቶ አብነት ፍቃዱ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል የመንግሥት፣ የማኅበረሰቡና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም ከኢኮኖሚ፣ ከባህልና ከህግ ተፈጻሚነት አንጻር የሚታየውን ኢፍትሀዊነት መቅረፍ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ዓለማቀፋዊ ገጽታ ስንመለከት 38.4 ሚሊየን ሰዎች ቫይረሱ በሰውነታቸው የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 25.6 ሚሊየን ወይም 66% የሚሆኑት በአፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል፡፡

በመርሀ-ግብሩ በመገኘት  የህይወት ልምዳቸውን ያካፈሉት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኘው ወ/ሮ አዲስ ኪዳን አስፋው ማኅበረሰቡ ስለ በሽታው በቂ ግንዛቤ ያለው ቢሆንም ተመርምሮ ራሱን ለማወቅ ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን እና አሁንም አድሎና ማግለሉ እንዳለ መሆኑን በተለያየ ጊዜ ያገጠማቸውን ገጠመኝ በማንሳት ገልጸዋል፡፡